Friday, 03 May 2024

ፖርኖግራፊ ምንድን ነው?

Posted On %AM, %20 %048 %2018 %03:%Jun Written by
ፖርኖግራፊ ምንድን ነው? Hanny Naibaho

ከፓርኖግራፊ ሱስ መውጣት ይቻላል!

ክፍል አንድ - ፖርኖግራፊ ምንድን ነው? 

በአንድ ወቅት ‘ጉግል’ አለም ላይ አብዝተው ወሲብ (Sex) የሚለውን ቃል ፈልግልን ከሚሉኝ 5 ሐገራት መካከል እናንተ ኢትዮጵያውያን ዋነኞቹ ናችሁ ብሎን ነበር። ይህ የሚያሳየን በሐገራችን እጅግ በጣም ብዙ ሰው የፖርኖግራፊ ተጠቃሚ  ወይም በፖርኖግራፊ ሱስ የተጠቃ መሆኑን ነው። ይህ ሱስ እንደሌሎች ሱሶች በግልጽ በሱሰኛው ላይ የማይታይ በመሆኑ እንዲሁም በማህበረሰባችን ውስጥ ስለ ጉዳዩ አሳሳቢነት በቂ መረጃ ስለሌለ የተጠቂዎች ቁጥር እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ ይገመታል። 

በቅድሚያ ግን ፖርኖግራፊ ምንድን ነው? 

ፖርኖግራፊ ቃሉ የተገኘው ‘πορνογραφία’ (pornographia) ከሚል የግሪክ ቃል ሲሆን በጥንት ጊዜ የቃሉ ትርጉም ስለ ሴተኛ አዳሪ ግልጽ በሆነ መንገድ የሚያትት ማናቸውም አይነት የስነ ፁህፍ ወይም የስነ ጥበብ ስራ ማለት ነው። ነገር ግን በአሁኑ ዘመን ይህ ከጽሁፍ እና ስዕል ወደ ቪዲዮ ምስል ማደጉን እናያለን። ማንኛውም የወሲብን ስሜት የሚቀሰቅሱ ወሲባዊ ታሪኮች፣ ፊልሞች፤ ፎቶግራፎች እንዲሁም የቃላት ልውውጥ ፖርኖግራፊ ይባላል።  በአሁኑ ወቅት ሰዎች ፖርኖግራፊ ለማየት ለዚህ ከተዘጋጁ ልዩ ድህረ ገፆች ባሻገር ለዚህ አላማ ባልተዘጋጁ የማህበረሰብ መገናኛ ድህረ ገፆች ማለትም ቴሌግራም፤ ትዊተር፤ ፌስቡክ የመሳሰሉትን በመጠቀም ለፖርኖግራፊ ሱስ ተጋላጭ ይሆናሉ።  በዘመናችንም ፖርኖግራፊ በቀላሉ ሊገኝ የሚችል መሆኑም ሱሱ እንደወረሽኝ እንዲዛመት አድርጎታል። ፖርኖግራፊ ሰዎችን በቀላሉ ሱሰኛ የማድረግ አቅም ያለው ሲሆን ሲጋራ፣ ጫት እና የተለያዩ ዕፆች  ሊያደርሱት ከሚችሉት ጉዳት በላይ ከባድ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል በግልጽ ለማየት ተችሏል።

ስለ ፖርኖግራፊ ጥናቶች ምን ይላሉ?

  • ስለፖርኖግራፊ የተሰሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ብዙውን ጊዜ ሰዎች ለፖርኖግራፊ ተጋላጭ የሚሆኑት ከ11 ዓመታቸው ጀምሮ ነው።
  • በኢንተርኔት ውስጥ ከሚገኘው ወደ ግማሽ የሚሆነው መረጃ ፖርኖግራፊ ወይም ከፖርኖግራፊ ጋር ተያያዥ የሆነ መረጃ ነው።
  • በየቀኑ ኢንተርኔት ከሚጠቀሙ ሰዎች መካከል 25% የሚሆኑት ፖርኖግራፊ የሚመለከቱ ናቸው።
  • ከኢንተርኔት ላይ ከሚወርዱ ቪዲዮዎች መካከል 35% የሚሆነው ከፖርኖግራፊ ጋር የሚገናኙ ናቸው ።
  • 34%  የሚሆኑት የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ሳይፈልጉት በማስታወቂያዎች በራሳቸው ብቅ በሚሉ ሌሎች መረጃዎች  ምክንያት ለፖርኖግራፊ ይጋለጣሉ። 
  • አለም ላይ ካሉ ድህረ ገጾች መካከል 12% የሚሆነው የፖርኖግራፊ ገጾች ነው።
  • በአለማችን ላይ ከፍተኛ ገንዘብ ከሚያገኙ ሰዎች መካከል በፖርኖግራፊ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉ ሰዎች ይገኙበታል። 
  • በሰሜን ኮሪያ በሐገሪቱ ውስጥ ፖርኖግራፊ ነክ የሆኑ ነገሮችን ማሰራጨትም ሆነ ማየት በሞት የሚያስቀጣ ነው።

ለምሳሌነት የጠቀስኩላችሁ እነዚህ ሃቆች ጉዳዩ ምን ያህል ትኩረት የሚያሻው መሆኑን ያሳያሉ። ይህ በሀገራችን ብዙ የማይደፈር ርዕስ ቢሆንም ትውልድን ራሳችንንም ለማዳን ስንል ደፍረን ልንነጋገርበት ወስነናል። 

ሰዎች ለምን ፖርኖግራፊ ይመለከታሉ?
ሰዎች ለምን ፖርኖግራፊን አዘውትረው ይመለከታሉ? ችግሩን መለየት በራሱ የመፍትሄው አንድ አካል ነው የሚለውን መርህ ይዘን ከብዙዎቹ ምክንያቶች ጥቂቶቹን ለመመልከት እንሞክር።

1. ደስታን ፍለጋ

ለዚህ ጥያቄ ግልፅ የሆነውና የመጀመሪያው ምላሽ ሰዎች ማንኛውንም አይነት ፊልም እራሳቸውን ለማዝናናት እንደሚመለከቱት ሁሉ ፖርኖግራፊንም የሚያነቃቃቸው እና ደስ የሚያሰኛቸው ነገር ከመፈለግ አንፃር ማየታቸው ነው። ከሰው መሰረታዊ ፍላጎቶች ውስጥ አንዱ ወሲብ እንደመሆኑ ሰዎች ይህንን ፍላጎት በተገቢው ሆነ ተገቢ ባልሆነ መልኩ ለማሟላት፤ በገሀዱ አለም እራሳቸው ያላደረጉትን ወይም የማያረጉትን ነገር ግን ስሜታቸው የሚፈልገውን ነገር አይተው በምናባቸው ተሳታፊ ለመሆን ፖርኖግራፊን ይመለከታሉ። 

2.  ጭንቀት/ድብርት


ብዙውን ጊዜ በድብርት እና በጭንቀት ውስጥ ያሉ ሰዎች በፖርኖግራፊ ሱስ የሚጠቁ መሆናቸውን ጥናቶች ያሳያሉ። በአብዛኛው በፖርኖግራፊ ብቻ ሳይሆን በሌላም የዕፅ ሱሶች የሚያዙ ሰዎች ሱስ የሆነባቸውን ድርጊት ደጋግመው እንዲያረጉ ሚገፋፋቸው ወሲባዊን ደስታን ለማግኘት ያላቸው ፍላጎት ሳይሆን ውስጣቸው ከሚሰማቸው የስሜት መዋዥቅ ማለትም ጭንቀት፣ ድብርት፣ ሀዘን፣ ፍርሃት እና ሀፍረት ለማምለጥ ነው። ስለዚህ በሕይወታቸው ከባድ ጭንቀት ያለባቸውና ያልፈቱት አስጨናቂ ነገር በልባቸው ያለባቸው ሰዎች ሃዘናቸውን ለመርሳትና ጊዜያዊ ደስታ ለማግኘት ይጠቀሙበታል። በስራ ቦታቸው ላይ ፖርኖግራፊ የሚመለከቱ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ስራቸውን እየጠሉት የሚሰሩ መሆናቸው ለማወቅ ተችሏል።


3. ብቸኝነት


ብዙውን ጊዜ ብቸኝነትን የሚያዘወትሩ በተለያየ ምክንያት ከሰዎች ጋር ህብረት ማድረግ የማይችሉ ሰዎች በዚህ ሱስ ሊጠቁ እንደሚችሉ ጥናቶች ያሳያሉ።

4. በጓደኛ ግፊት


በአብዛኛው ታዳጊዎች እና ወጣቶች ስለ ወሲብ ምንነት ለማወቅ ካላቸው ጉጉት የተነሳ ወደ ፖርኖግራፊ ሊሳቡ ይችላሉ።  ብዙዎች ወደ ሚያደርጉት ነገር ወይም ከዚያም ባለፈ በደፈናው ‘አታርጉ!’ የሚባሉ ነገሮችን የመሞከር ዝንባሌ በወጣቶች ይስተዋላል ። ታዳጊዎችና ወጣቶችም በጓደኞቻቸው ግፊት ወደዚህ ህይወት በቀላሉ ሊሳቡ ይችላሉ። ለ10 አመት ያህል በፖርኖግራፊ ሱስ ውስጥ ያለች አንዲት እህት እንዴት ወደዚህ ሱስ እንደገባች እንዲህ ስትል አጫውታኛለች።  “የዪኒቨርስቲ ተማሪ እያለሁ ዶርም ውስጥ ጓደኞቼ ተሰብስበው ፖርን ይመለከቱ ነበር። እኔ ግን ሁሌም እቃወማቸው ነበር። ከሆነ ጊዜ በዋላ ግን ሳላስበው እነሱን መቀላቀል ጀመርኩ። ከዚያ በኋላ ከነሱ የባስኩ ተመልካች ሆንኩኝ። 


5. ሱስ


አንዳንድ ሰዎች ፖርኖግራፊን በተለያየ ምክንያት አንድ ጊዜ ወይም ከዚያ በላይ ከተመለከቱ በኋዋላ ሱሰኝነትን ያዳብራሉ።  ሱስ ማለት ፈልገን የገባንበት ኋላ ግን እየጠላነውም ቢሆን የምናደርገው ነገር ነው። ማንኛውም ሱስ ሲጀመር በፍላጎት ሲሆን የሚቀጠለው ግን ያለ ፍላጎት ሊሆን ይቻላል። ፖርኖግራፊ ልክ እንደማንኛውም አደንዛዥ ዕጽ ሰዎችን ሱሰኛ የማድረግ ከፍተኛ አቅም አለው። በአንድ ወቅት ስለ ፖርኖግራፊ ሱስ ዶክተር ስዩም ያሉትን ልዋስ፤
“ብዙዎች ፖርኖግራፊ ሳያዩ መተኛት በማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ ሆነው ሱስ አይሆንም ብሎ የመናገር ድፍረት አላቸው:: ነገር ግን ፖርኖግራፊ ከሌሎች ሱሶች ባልተናነሰ እንዲያውም በበለጠ መልኩ ወደ ሱስነት ያድጋል። አንድ ሰው ፖርኖግራፊ ሲመለከት ደሙ ውስጥ የሚለቀቁ ቅመሞች (hormons) አሉ፤ እነዚህ ቅመሞች አንድ ሰው ኮኬንና ሄሮዊን የሚባሉትን አደዛዥ ዕፅ ሲጠቀም በደሙ ውስጥ የሚለቀቁ ቅመሞች ናቸው። እኚህን ዕጾች ስንወስድ ደማችን ውስጥ የሚለቀቁት ቅመሞች ፖርኖግራፊ በምናይበት ጊዜ ከተለቀቁ ፖርኖግራፊ ሱስ አይሆንም ማለት አንችልም። ሱስ ለመባል የግድ በአፍ በኩል ወደ ውስጣችን መግባት የለበትም። አሁን ባለን መረጃ ‘Pornography is not like a drug, it is a drug’ (ፖርኖግራፊ አንደ አደንዛዣ ዕፅ ሳይሆን እራሱ አደንዛዥ ዕፅ ነው) እንዲያውም መልከ ብዙ ዕፅ ነው። ሰው ፖርኖግራፊ ሲያይ ብዙ ዕፅ በአንድ ላይ እንደወሰደ ይቆጠራል።  አንድ የኒዩሮ ሳይንቲስት (neuroscientist) ባለሙያ በፖርኖግራፊ ለመለከፍ የሚፈጅበትን ጊዜ ሲናገሩ አንድን ምስል ለግማሽ ሰከንድ ካየን በኋላ በሚቀጥሉት 5 ና 10 ደቂቃ ውስጥ አንጎላችን ውስጥ መሰረታዊ የሆነ የቅርጽ ለውጥ (nerve restriction) ይፈጠራል።  ይሄ አይነት ለውጥ ልክ አንድ ሰው አደጋ ሲደርስበት የሚፈጠረውን የቅርጽ ለውጥ አይነት ነው። በፖርኖግራፊ ለመለከፍ የሰከንድ 1/3ኛ ይበቃል እንደማለት ነው:: አስተውላቹ ከሆነ ለሰከንድ ያየነው የፖርኖግራፊክ ምስል ለአመታት ከአይምሮአችን አይወጣም። ለምን ካላችሁ ‘epimerphine’ በተባለው ‘ሆርሞን’ ምክንያት እንዳይጠፋ ሆኖ ተቀርጿል:: ከዚህም የተነሳ ከአመታት በኋላ እንኳን አይረሳም። በዚህም ምክንያት ‘በቃ አይኔንም ስከድን ስተኛም በመንገድ ላይ ስሄድም የሚመጣብኝ እሱ ነው’ እያሉ በመንፈስ ጭንቀት የሚሰቃዪ ወጣቶች ገጥመውኛል።” 

ከዚህ የምንረዳው በቀላሉ የሚጀመር ነገር እንዴት ወደ ትልቅ ሱስ ሊያድግ እንደሚችል ነው። 

በሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ፣ ስለ ፖርኖግራፊ ሱስ ምልክቶች እና መዘዞች በክፍል ሁለት የምናይ ይሆናል። 


Download the series in PDF (166KB)


በፖርኖግራፊና ግለ ወሲብ/Masturbation/ ሱስ ተይዛቹ የምትጨነቁ ወገኖቻችን በማንኛውም ጊዜ ልንረዳቹ ዝግጁ ነን። በ+251945000005 ላይ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ 4 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት ድረስ ይደውሉልን። ከኢትዮጵያ ውጭ ከሆኑ በቫይበር፣ በቴሌግራም፣ በኢሞ፣ በዋትስአፕ እና በላይን ሊያገኙን ይችላሉ።

Last modified on %PM, %05 %630 %2018 %17:%Jul
Ermias Kiros

Ermias Kiros has a bachelors degree in theology and social anthropology, and he is currently doing his Masters in Counseling Psychology. Currently, he works as inspirational public speaker and counselor.

https://www.facebook.com/ermias.kiros.1

ፀሀይ ግባት እና ወጀብ

“እግዚአብሔር ለክብሩ የተከላቸው የጽድቅ ዛፎች እንዲባሉ ለጽዮን አልቃሾች አደርግላቸው ዘንድ፥ በአመድ ፋንታ አክሊልን፥ በልቅሶም ፋንታ የደስታን ዘይት፥ በኀዘ...

Michelle Zombos - avatar Michelle Zombos

ጨርሰው ያንብቡ

መጽሐፍ ቅዱሳችንን ችላ ምንልባቸው ምክንያቶች

የእያንዳንዱ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ ከመነበብ ብዛት ያረጀ፤ በየቦታው የተሰመረበት፤ በተለያዩ ቀለማት የተፃፉ መንፈሳዊ ሃሳቦችን የያዘ ማስታወሻ አብሮት ያለ ...

Tony Reinke - avatar Tony Reinke

ጨርሰው ያንብቡ

 

The views and opinions expressed on Daily Injera are solely those of the original authors and our contributors. These views and opinions do not necessarily represent Daily Injera or our Staff.

Newsletter

Subscribe to our newsletter. Don’t miss any article, devotionals or wallpapers.

We do not spam!

You're automatically subscribed to bi-weekly articles and daily devotionals. You can customize your subscription settings here.