Thursday, 25 April 2024

ክርስቲያን ተማሪዎች በተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ እንዲማሩ የሚያበረታቱ 5 ምክንያቶች

Posted On %PM, %05 %780 %2018 %20:%Oct Written by

ትምህርት ሚኒስቴር (የሃገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ) ባሳለፍነው አርብ መስከረም 24 ወደ መንግስት ዩኒቨርሲቲዎች (ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት) የተማሪዎችን ምደባ ይፋ አድርጓል። እንደ ምንጊዜውም ሁሉ ለአንዳንዶች ሲመደብላቸው ለሌሎች ደግሞ ተመድቦባቸዋል። እንደእውነታው ከሆነ ብዝሃው ወደሚፈልግበት ቦታ አይደለም የሚሸኘው። ከዚህ መነሻ ብዙ ክርስቲያን ተማሪዎችም ግር ሲሰኙ እና በተመደቡበት ዩኚቨርሲቲ ለመማር እና ላለመማር ፣ ለመሄድ እና ላለመሄድ እንዲሁም ለመቀየር እና ላለመቀየር ሲያመነቱ ይታያል። ይህ የሚጠበቅ ስሜት ሲሆን እዚህ ላይ ደግሞ የእግዚአብሔር ሃሳብ እና ፈቃድ ምን ሊሆን እንደሚችል እንዲጠይቁ ማበረታታቱ መልካም ነው።

የጭንቅ ጊዜያት

የ12ኛ ከፍል ብሔራዊ ፈተና ከወሰድኩ በኋላ የዩኒቨርሲቲ ምርጫ ለመወሰን እጅግ ከብዶኝ ነበር። አስቀድሜ ኢንጅነሪንግ ማጥናት ነበር የፈለግሁት ፤ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ።

ነገር ግን ውጤት ከመጣ በኋላ በአንዳንድ ሰዎች ምክር ምርጫዬን ወደ አዲስ አበባ አዞርኩት (በድጋሜ አስተካከልኩ)።

በዚህ ግን አላበቃም ከሳምንት በኋላ በተጨማሪ አሁንም ከኢንጂነሪንግ ወደ ሕክምና ቀየርኩ። አሁንም አልጣመኝም ከሳምንት በኋላ ወደ ኢንጂነሪንግ ቀየርሁት። ምን አለፋችሁ እንዲህ ምርጫዬን እየቀያየርሁ ሳስቸግር የትምህርት ቤታችን የሪከርድ ክፍል ኋላፊው ምንም እንኳን ለተማሪዎች ተከለከለ ቢሆንም ጭንቀቴን ተረድቶ ባሻኝ ጊዜ እንዳስተካክል የትምህርት ቤቱን ፓስወርድ ሰጠኝ።

በቃ ልቤ እስኪያርፍ ድረስ ቀያየርሁ። በመጨረሻም ሕክምና እና አዲስ አበባ ሞልቼ አረፍኩት። የሆነው ሆኖ የፈለግሁት ደረሰኝ። ዛሬም ላይ ቆሜ ታዲያ ሌሎቹን አማራጮች መለስ ብዬ አጤናቸዋለሁ። አዳማ – ኢንጂነሪንግ!

በአርብ ለቱ ምደባ ምናልባት ብዙዎች የጭንቅት ጊዜ አሳልፈው እንደነበር አይካድም። ይህም ሆኖ ታዲያ ብዙ ተማሪዎች የፈለጉበት አልደረሳቸው ይሆናል። እኔም ብሆን በብዙዎች ጫና ነው ወደዚህ የትምህርት ዘርፍ እና ዩኒቨርሲቲ ምርጫ የገባሁት። ነገር ግን ዛሬ ላይ ብዙ ነገሮችን ተምርያለሁ። አሁን ባለሁበት ቦታ መኖሬ ለእግዚአብሔር ክብር እንደሆነ ተረድቻለሁ። ደግሞም የፈራኋቸውንና የጠላኋቸውን እግዚአብሔር ለመልካም ቀይሮ ሲሰራባቸውና ስወዳቸው አስተውያለሁ።

ግን ከዚህም በላይ ክርስትያን ተማሪዎች የተመደቡበትን ዩኒቨርሲቲ ወደው እንዲማሩ የሚያበረታቱ ምክንያቶች አሉ።

ከ«እኔ» ያለፈ ምክንያቶች

ትምህርት ሚኒስቴር እንደገለጸው ከሆነ ያለፈውን አመት የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ከወሰዱ 285,000 (ሁለት መቶ ሰማንያ አምስት ሺህ) የሚበልጡ ተማሪዎች መካከል 137,136 (አንድ መቶ ሰላሳሰባት ሺህ አንድ መቶ ሰላሳ ስድስት) የሚደርሱቱ አልፈው ወደ 32 የ መንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበዋል1

እንግዲህ ይህ ቁጥር በአሁኑ ሰአት ያለውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ይወክላል ብለን ከተነሳን እና መቼም የ2010 የሕዝብ ቆጠራ ገና አልደረሰምና እየታየ ካለው የፕሮቴስታንት ሕዝብ እድገት አንጻር ከሐገሪቱ ሕዝብ 20% ይሸፍናል ብለን ካሰብን ዘንድሮ ወደ ዩኒቨርሲቲ ከተመደቡት 137,136 ተማሪዎች መካከል 27,427 (ሃያሰባት ሺህ አራት መቶ ሃያ ሰባት) የሚደርሱት ተማሪዎች የወንጌላውያን እምነትን ይከተላሉ ማለት ነው።*

ልብ እንበል 27,427 የሚደርሱ ዩኒቨርሲቲ ሊገቡ ያሉ ተማሪዎች የወንጌላውያን እምነት ተከታዮች ሃገሪቱ ውስጥ በሚገኙ በ 32 ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ይመደባሉ።አማካይ እንስራ ካልን አንድ ዩኒቨርሲቲ 857 አዳዲስ ፕሮቴስታንት ተማሪዎችን ያገኛል ማለት ነው። ይህ ታዲያ ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች እኩል ቢቀበሉ ብለን አስበን ነው። (እንደሚታወቀው የሁሉ አቀባበል ይለያያል)*

ታዲያ ይህ ሁሉ ትርጉሙ ምንድን ነው? እነዚህ 857 ተማሪዎች እግዚአብሔር እንደ ዳንኤል በባቢሎን ያስቀመጣቸው ምስክሮቹ ቢሆኑስ? እንደ አስቴር በንጉስ ቤት የላካቸውና አንድ ቀን ሊጠቀምባቸው ያሉ ሰዎች ቢሆኑስ? እንደ ዮሴፍ ግብጽን ለመታድግ እንዲሁም ለክርስቲያን ወንድሞቻቸው እረፍት እና መልስ ለመሆን የተላኩስ ከሆነ? ማን ያውቃል?

ከእነዚህ ከ857 ተማሪዎች መካከል ሆናችሁ በተመደባችሁበት ዩኒቨርሲቲ ደስተኞች ካልሆናችሁ እንዲሁም ለመቀየር ወይም ለመቅረት እያሰባችሁ ከሆነ ሃሳባችሁን ከመተግበራችሁ በፊት ወደ ተመደባችሁበት ዩኒቨርሲቲ እንድትሄዱ የሚያበረቷቷችሁን ከእናንተ ያለፉ ምክንያች እንድታስቡ እጠይቃለሁ።

ሁሌም ከ«እኔ» ወጣ ያለ ምክንያት ከእኛ በላይ ታሪክ ሰርተን እንድናልፍ ያደርገናል።

1) እግዚአብሔር በአማኞች ሕይወት ሉዐላዊ ነው!

የትምህርት ሚኒስቴር በሃይማኖት እየከፋፈለ ምደባ አያደርግም። እግዚአብሔር ግን የልጆቹን መድረሻ ያቅዳል። በክርስቶስ ኢየሱስ ዳግም የተወለደ ሁሉ እግዚአብሔር በሉዐላዊነት በሕይወቱ እንዲሰራ ፈቅዶለታል። ‹‹እግዚአብሔርን ለሚወዱትና እንደ ሐሳቡ ለተጠሩት ነገር ሁሉ ተያይዞ ለበጎ እንዲሰራ እንደሚያደርግላቸው እናውቃለን›› (ሮሜ 8፡28 አመት) ይላል። እግዚአብሔርን ለሚወዱት እና እንደሃሳቡም ለተጠሩት እግዚአብሔር ጣልቃ ገብነት አለ!

ስለዚህ የዩኒቨርሲቲ ምደባው ከሰይጣን ሳይሆን ከእግዚአብሔር እንደሆነ ልንረዳ ይገባል። ‹‹ሰይጣን ነው ይህን ያደረገው›› ብለን ካሰብን ሰይጣን በእግዚአብሔር ልጆች ሕይወት ይህንን የማድርግ ስልጣን ካለው ታዲያ እስከዛሬ ድረስ አማኞችን ለምን በሕይወት ያቆያቸዋል (ይሄ ሁሉ ጊዜ ስራውን ሲያፈርሱበት ኖረው ማለቴ ነው)? ሰይጣን የአማኝን እድልፈንታ የመወሰን አቅም የለውም!

አንዳንዶች የተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ እጅግ በጣም ሞቃታማ ፣ በረሃማ ወይ ደግሞ ከባድ ብርድ ያለበት ደጋማ ቦታ ነው። ይህ እንደሰው ከባድ የሚመስል ቦታ ከሰይጣን ከሆነ እስከዛሬ መኖራችን ሰይጣን ራርቶልን ነውን? አይደለም! ስለዚህ የዩኒቨርሲቲ ምደባው ላይ እግዚአብሔር ሉዐላዊ ጣልቃገብነት እንዳለ መረዳት አለብን።

2) እግዚአብሔር ዓላማ አለው!

የዝሆኑን ምሳሌ ብዙዎች ያውቁታል። ስምነት አይነ ስውሮች የአንድን እንስሳ በመንካት ብቻ ምን እንደሆነ እንዲናገሩ ተጠየቁ። እነስሳው ዝሆን ነበር። ይህን ያወቀ ይሸለማል።

ከአይነስውሮቹ የመጀመሪያው ታዲያ የዝሆኑን ኩምቢ ነካና «ትቦ ነው» አለ። ሌላው የዝሆኑን እግር ነካና «የተከመረ ጡብ ነው» አለ። ሌላኛው ደግሞ ሆዱን ነካና «ግንብ ነው» አለ። ቀጣዩ ጭራውን ነካና «ገመድ ነው»። አንዲህ እያለ ሌሎችም የመሰላቸውን ተናገሩ።

እነዚህ ሰዎች የነኩትን ቦታ ብቻ ቢናገሩም ሙሉውን እንስሳውን ያወቀ ግን አልነበረም። በሕይወት አንዳንድ ጊዜ እንዲህ እንሆናለን። እኛ የምንነካውን ብቻ ነው የምንናገረው፤ እግዚአብሔር ግን ሙሉውን ስዕል ያውቀዋል። እኛ አንዲቷን ነገር መዝዘን እናጉረመርማለን። እግዚአብሔር ግን የሙሉው ነገር መረጃ አለው።

ታዲያ እግዚአብሔር በልጆቹ ዩኒቨርሲቲ ምርጫ ላይ ጣልቃ ይገባል ካልን እንዴት አላማ አይኖረውም? በብዙ ጥፋት ቅጣት ላይ ለነበሩት እንኳ ከሰባ አመት በኋላ ሊጎበኛቸው «ለእናንተ ያለኝን እቅድ እኔ አውቃለሁ።… ዕቅዱም ፍፃሜው ያማረና ተስፋ የሚሰጥ፣ እናንተንም የሚጠቅም እንጂ የሚጎዳ አይደለም።›› (ት.ኤር 29፡11) ያለ አምላክ እንዴት በክርስቶስ ኢየሱስ ዳግም ለተወለዱ ልጆቹ እጅግ የሚልቅ መልካም ዕቅድ አይኖረውም? አለው እንጂ!

ከተማ ፈልገን ገጠር ወይንም ያለ ከተማ አካባቢ ደርሶንም ቢሆን አልያም ከወዳጆቻችን ተነጥለን ሌላ ቦታ ከደረሰን ልናውቀው የሚገባው ነገር፣ እግዚአብሔር ሉዐላዊ በሆነ ፈቃዱ መልካም እቅዱን በሕይወታችን ሊፈጽም እንደሚወድ ነው። ታዲያ አማኝ ክርስቲያኖች ወደ ተመደቡበት ሃገር ሄዶ በመማር የእግዚአብሔርን መልካም አላማ እንዲያጣጥሙ አበረታታለሁ።

ግን ይህ እግዚአብሔር ዓላማ ምንድን ነው? በእያንዳንዱ ሰው ሕይወት ላይ ለውን ልዩ እግዚአብሔር አላማ እንዲህ ብለን መግለጽ ባንችልም ልናውቀው የሚገባን ግን የእግዚአብሔር አላማ ምንም ይሁን ምንም መልካም እንደሆነ ነው። በዩኒቨርሲቲ ሕወት ውስጥ ካለፉ ብዙ ሰዎች እንደምንማረው በዩኒቨርሲቲ ምደባዎች እግዚአብሔር ልዩ ልዩ አላማዎቹን በልጆቹ ሕይወት ሊፈጽም ይችላል።

3) እግዚአብሔር በወደደው ስፍራ ሊሰራን ይፈልጋል!

‹‹ስለዚህ አባብላታለሁ ወደ ምድረ በዳም አመጣታለሁ፤ ለልብዋም እናገራለሁ›› (ት.ሆሴ 2፡16)

እግዚአብሔር በልብዋ ከእግዚአብሔር ላፈነገጠችው እንዲሁም ከእግዚአብሔር ይልቅ ጣኦቶችን ላስበለጠችው ለሰሜኗ እስራኤል በነብዩ ሆሴዕ በኩል ሲናገር ‹‹አባብላታለሁ›› ደግሞም ‹‹ወደ ምድረ በዳም አመጣታለሁ፤ ለልብዋም አንገራለሁ›› አለ። እግዚአብሔር ሕዝቡን ለማባባበል እና ለልባቸው ለመናገር ምድረበዳ የተሻለ ስፍራ እንደሆነ አስቧል። ምድረበዳን ማን ይወዳል?

ብዙዎች በትምህርት ቤት ምደባ ምናልባት ከወላጆቻቸው ርቀው ሊሆን ይችላል። ጓደኛ የሚሉት ከጎናቸው ላይኖር ይችላል። በአጠቃላይ ‹‹ምድረ በዳ›› ደርሷቸው ሊሆን ይችላል። ይህ ‹‹ምድረበዳ›› እግዚአብሔር ለልባቸው ሊናገራቸው እናም በቅዱሱ መንፈስ በኩል የመቅደሱን ስራ የሚሰራበት የተመቻቸው ስፍራ ቢሆንስ?

ለመሆኑስ ስንቶች ነን የሃይስኩል ቆይታችንን እግዚአብሔርን በሚያስከብር ሕይወት ያጠናቀቅነው? ይህ መልስ በግል ይመለስ!

አስታውሳለሁ አንዲት በጣም የማከብራት እህት ስለ ትምህርቷ ስትነግረኝ ‹‹ሁሉን አጥቼ ፤ ጌታን አገኘሁ›› እንዳለችኝ። ይሄ የዩኒቨርሲቲ ምደባ ብዙዎች አለኝ የሚሉትን ሁሉ አጥተው ጌታን ግን የሚያገኙበት አጋጣሚ ቢሆንስ? ከወላጅ ጥላ ስር ወጥተው እግዚአብሔርን በግላቸው ለማወቅ እድል የሚያገኙበት ጊዜስ ቢሆን?

ይህንን ተግባሩን የሚፈጽምበት የካምፓስ ሕብረቶች (ፌሎሺፖች) አሉ። የብዙ ታላለቅ የእግዚአብሔር ሰዎች ሕይወት የተቀየረው ፤ ብዙዎች ጌታን ያገኙት ፣ ብዙዎች በመንፈሳዊ ህይወታቸው ያደጉት አና የተሰሩት በእነዚህ ሕብረቶች ነው። እግዚአብሔር ተማሪዎች በተመደቡበት አካባቢ ባሉ ህብረቶች ሕይወታቸውን ሊያድስ ፍልጎ ከሆነስ? ‹‹አባብላታለሁ›› ፣ ‹‹ለልብዋም እናገራለሁ››

4) እግዚአብሔር በእኛ ሌሎችን ሊ ታደግ ይፈልጋል

ሌላው ከ‹‹እኔ›› ወጣ ያለው ምክንያት ስለሌሎች እንድናስብ ያስገድደናል። የክርሰቲያኖች ሕይወት የተልዕኮ ሕይወት ነው። በምድር ላይ በተልዕኮ ላይ ያለን ሰማያዊ ዜጎች ነን። ይህን ሰማያዊ አጀንዳ እስከአለም ዳርቻ እስከ አለም ፍጻሜ ድረስ ይሄዳል(ማር 16፡15 ፣ ማቴ 28፡20)።

በጆሽዋ ፕሮጀክት የቅርብ ጊዜ መረጃ መሰረት በኢትዮጵያ ከሚኖረው ወደ 102,000,000 (ከመቶ ሁለት ሚልዮን ሕዝብ) ባላይ ውስጥ 20,000,000 (ሃያ ሚልዮን) የሚደርሰው ሕዝብ በወንጌል ያልተደረሰ ሕዝብ ነው2። ቀደም ብለን ካየናቸው 27,427 (ሃያ ሰባት ሺህ አራት መቶ ሃያ ሰባት) አዳዲስ ዩኒቨርሲቲ ገቢ ተማሪዎች ግማሹ ወይንም 13,714ቱ ወዳልተደረሱት ሃያ ሚልዩን ሕዝቦች ቢበተኑ አንዱ ክርስትያን ተማሪ 1458 ፈጽመው ወንጌል መስማት ያልቻሉ ሰዎችን በወንጌል ይደርሳል ማለት ነው።*

ይህ ቁጥር (ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገባው አማኝ ቁጥር) ተመሳሳይ ከሆነ ከአስር አመት በኋላ አንድ አዲስ ገቢ ክርስትያን ሰባ ሶስት ወንጌል ያልሰሙ ሰዎችን ብቻ ነው የሚደርሰው። እንዲህ እያልን ምድራችንን በወንጌል ማዳረስ እንችላለን። እግዚአብሔር ተማሪዎችን ለዚህ አስቦ ቢሆንስ?

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያልተደረሱትን ለመድረስ ትልቅ ሃይል እንደሆኑ ብዙዎች ይመሰክራሉ። ብዙ የካምፓስ ሚሽን ሪፖርቶች ይደርሱኛል (ከተለያየ ዩኒቨርሲቲ) ። እግዚአብሔርን ስለያንዳንዱ አከብራለሁ! እግዚአብሔር በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተጠቅሞ ለብዙዎች እረፍት ፣ ሰላም እና የዘላለምን ሕይወት እየሰጠ ነው። ይህ ሆነው ግን ‹‹እሺ›› ብለው ታዘው ወደ ተመደቡበት ዩኒቨርሲቲ የገቡ ተማሪዎችን ስላገኘ ነው።

ከዚህም ባለፈ ክርሰትያን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በተመደቡበት ቦታ ለሌላ ክርሰትያን እረፍት እና መልስ እንዲሁም መፈወስ ምክንያት ሲሆኑም ተመልክቻለሁ። ለአከባቢ መለወጥ ፣ እንዲሁም በዚያ አካባቢ ላሉ አብያተ ክርሰትያነናት መነቃቃት የሆኑም የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አውቃለሁ። እግዚአብሔር ዛሬም የሚታዘዙትን ካገኘ በእርሱ ታሪክ ለመስራት ዝግጁ ነው!

5) እግዚአብሔር መስዋዕትነትን ያለማምደናል!

‹‹እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ በጎ ወታደር፣ ከእኛ ጋር መከራን ተቀበል›› (2ኛ ጢሞ 2፡3)

በዚህ ግለኝነት እንደ ጀብዱ በአደባባይ ብዙ ደጋፊ በሚያስገኝበት በዚህ ዘመን ለሌሎች መስዋእት እንድንሆን በእግዚአብሄር ልጅ ምሳሌ ተጠርተናል። እንደውም ታዞ ዩኒቨርሲቲ የመሄድ ጉዳይ የመስዋእትነት ጉዳይም ነው!

ይህ እንግዲህ ከመንፈሳዊው አንጻር ነው። በምድራዊው አስተሳሰብ ሩቅ የተመደበው ውጤቱ ደከም ስላለ ነው ሊባል ይችላል። እንደ መንፈሳውያን ሰዎች የምናስተውለው ግን እግዚአብሔር በሉዐላዊ ፈቃዱ ልዩ አላማውን በእኛ የሚፈጽመው እኛ ዋጋ ለመክፈል ፈቃደና ስንሆን ነው። ይህንን ዋጋ መክፈል የምንለማመደው ታዲያ ቤተሰባችን ጋር ተመችቶን ስንኖር ሳይሆን ከጓደኞቻችን ጋር እየተገናኘን ማታ ማታ ካፌ ስንቀመጥ ሳይሆን እግዚአብሔር በመደበን ቦታ ለእግዚአብሔር አላማ ስንገኝ ነው!

ስለዚህም በተመደብንበት ቦታ በመሄድ ዋጋ የምንከፍል በጎ የክርስቶስ ኢየሱስ ወታደሮች እንሁን። በረሃ ቢሆን ተቋቁመን እግዚአብሔርን ዓላማ እናስፈጽም እኛም በትምህርታችን እንበርታ። ውርጭ ቢሆን ጥርሳችንን ነክሰን ፊታችን የተሳለውን መስቀል እየተመለከትን እግዚእብሔር ያዘጋጀልንን ለመያዝ ወደፊት እንዘርጋ እንጂ አማራጮችን አናፈላልግ!

ማጠቃለያ፡

እነዚህ ምክንያቶች አምናለሁ አንድ ትርጉም እንደሚሰጡ። በሕይወቴ ተገልጠው ሲጠቅሙ አይቻለሁ። ዛሬም ድረስ ሳስባቸው በአንድ በኩል የእኔ ምርጫ ስላልደረሰኝ እግዚአብሔርን ሳመሰግን በሌላ በኩል ደግሞ አብልጬ የጌታን አላማ በሕይወቴ እንድሻ ያበረታቱኛል። ሌሎችንም እንዲያበረታቱ ጸሎቴ ነው! መልካም የትምህርት ዘመን!


ማጣቀሻዎች

(1) National Education Assessment and Examination Agency

(2) Joshua Project

* ይህ ፅሁፍ በ2010 ዓ.ም የተፃፈ ስለሆነ አንዳንድ አሀዞች አሁን ካሉ መረጃዎች ጋር ሊለያዩ ይችላሉ።

Last modified on %PM, %05 %850 %2018 %22:%Oct
Naol Befkadu

Naol Befkadu Kebede (BTh, student of MA in Ministry and Medical Doctorate student at AAU) is the founder and contributor of Lechristian Blog, an online ministry that aims to redeem cultures for the glory of God and to inspire and encourage believers for the completion Great Commission. Naol has authored an Amharic book titled "ተነሺ ፤ አብሪ" (2015) that motivates young believers for a meaningful and radical life. 

lechristian.blogspot.com

መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ የሚረዱ ሁለት ጠቃሚ መንገዶች

መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ጠቃሚ እንደሆነ የሚያስረዱ ምክንያቶችን መናገር ላያስፈልጋችሁ ይችላል። ጠቃሚ መሆኑን ግን ጠንቅቃችሁ ታውቃላችሁ። ትንሽ ማበረታቻም ሊያ...

Andy Naselli - avatar Andy Naselli

ጨርሰው ያንብቡ

እግዚአብሔር ህዝቡን የሚመራባቸው አራት መንገዶች

እግዚአብሔር ህዝቡን በፍቃዱ ውስጥ ሊመራባቸው የሚችላቸው ቢያንስ አራት መንገዶች ይታዩኛል።

John Piper - avatar John Piper

ጨርሰው ያንብቡ

 

The views and opinions expressed on Daily Injera are solely those of the original authors and our contributors. These views and opinions do not necessarily represent Daily Injera or our Staff.

Newsletter

Subscribe to our newsletter. Don’t miss any article, devotionals or wallpapers.

We do not spam!

You're automatically subscribed to bi-weekly articles and daily devotionals. You can customize your subscription settings here.